1
ከጦር ዘረፋ ገንዘቦች ይጠይቁሃል፡፡ «የዘረፋ ገንዘቦች የአላህና የመልክተኛው ናቸው፡፡» ስለዚህ አላህን ፍሩ፡፡ በመካከላችሁ ያለችውንም ኹኔታ አሳምሩ፡፡ አማኞችም እንደኾናችሁ አላህንና መልክተኛውን ታዘዙ በላቸው፡፡
2
ፍጹም ምእምናን እነዚያ አላህ በተወሳ ጊዜ ልቦቻቸው የሚፈሩት፣ በነሱም ላይ አንቀጾቻችን በተነበቡ ጊዜ እምነትን የሚጨምሩላቸው፣ በጌታቸውም ላይ ብቻ የሚመኩት ናቸው፡፡
3
እነዚያ ሶላትን ደንቡን አሟልተው የሚሰግዱ ከሰጠናቸውም ሲሳይ የሚለግሱ ናቸው፡፡
4
እነዚያ በእውነት አማኞች እነሱ ብቻ ናቸው፡፡ ለእነሱ በጌታቸው ዘንድ ደረጃዎች ምህረትና የከበረ ሲሳይም አላቸው፡፡
5
(ይህ በዘረፋ ክፍያ የከፊሉ ሰው መጥላት) ከምእምናን ከፊሉ የጠሉ ሲኾኑ ጌታህ ከቤትህ በእውነት ላይ ኾነህ እንዳወጣህ ነው፡፡
6
እነርሱ እያዩ ወደሞት እንደሚነዱ ኾነው በእውነቱ ነገር (በመጋደል ግዴታነት) ከተገለጸላቸው በኋላ ይከራከሩሃል፡፡
7
አላህም ከሁለቱ ጭፍሮች አንደኛዋን እርሷ ለናንተ ናት ሲል ተስፋ በሰጣችሁ ጊዜ፣ የሀይል ባለቤት ያልኾነችውም (ነጋዴይቱ) ለናንተ ልትኾን በወደዳችሁ ጊዜ፣ አላህም በተስፋ ቃላቱ እውነትን ማረጋገጡን ሊገልጽና የከሓዲዎችንም መጨረሻ ሊቆርጥ በሻ ጊዜ (የኾነውን አስታውስ)፡፡
8
(ይህንንም ያደረገው) አጋሪዎቹ ቢጠሉም እውነቱን ሊያረጋግጥ ክህደትንም ሊያጠፋ ነው፡፡
9
ከጌታችሁ ርዳታን በፈለጋችሁ ጊዜ «እኔ በሺህ መላእክት ተከታታዮች ሲኾኑ እረዳችኋለሁ» ሲል ለናንተ የተቀበላችሁን (አስታውሱ)፡፡
10
አላህም (ይኽንን ርዳታ) ለብስራትና ልቦቻችሁ በርሱ ሊረኩበት እንጂ ለሌላ አላደረገውም፡፡ ድልም መንሳት ከአላህ ዘንድ እንጂ ከሌላ አይደለም፡፡ አላህ አሸናፊ ጥበበኛ ነውና፡፡
11
ከእርሱ በኾነው ጸጥታ (በጦር ግንባር) በእንቅልፍ በሸፈናችሁና ውሃውንም በእርሱ ሊያጠራችሁ፣ የሰይጣንንም ጉትጎታ ከእናንተ ሊያስወግድላችሁ፣ ልቦቻችሁንም (በትዕግስት) ሊያጠነክርላችሁ፣ በእርሱም ጫማዎችን (በአሸዋው ላይ) ሊያደላድልላችሁ በእናንተ ላይ ከሰማይ ባወረደላችሁ ጊዜ (አስታውሱ)፡፡
12
ጌታህ ወደ መላእክቱ «»እኔ (በእርዳታዬ) ከእናንተ ጋር ነኝና እነዚያን ያመኑትን አጽናኑ፡፡ በእነዚያ በካዱት ልቦች ውስጥ ፍርሃትን በእርግጥ እጥላለሁ፡፡ ከአንገቶችም በላይ (ራሶችን) ምቱ፡፡ ከእነሱም የቅርንጫፎችን መለያልይ ሁሉ ምቱ፡፡ ሲል ያወረደውን (አስታውስ)፡፡
13
ይህ እነርሱ አላህንና መልክተኛውን ስለተቃወሙ ነው፡፡ አላህንና መልክተኛውንም የሚቃወም ሁሉ አላህ ቅጣቱ ብርቱ ነው፡፡
14
ይህ (ቅጣታችሁ ነው) ቅመሱትም፡፡ ለከሓዲዎችም የእሳት ቅጣት በእርግጥ አለባቸው፡፡
15
እናንተ ያመናችሁ ሆይ! እነዚያን የካዱትን ሰዎች (ለጦር) ሲጓዙ ባገኛችኋቸው ጊዜ ጀርባዎችን አታዙሩላቸው፡፡
16
ያን ጊዜም ለግድያ ለመዘዋወር ወይም ወደ ሠራዊት ለመቀላቀል ሳይኾን ጀርባውን የሚያዞርላቸው ሰው ከአላህ በኾነ ቁጣ በእርግጥ ተመለሰ፡፡ መኖሪያውም ገሀነም ናት፡፡ መመለሻይቱም ከፋች፡፡
17
አልገደላችኋቸውም ግን አላህ ገደላቸው፡፡ (ጭብጥን ዐፈር) በወረወርክም ጊዜ አንተ አልወረወርክም፡፡ ግን አላህ ወረወረ (ወደ ዓይኖቻቸው አደረሰው)፡፡ ለአማኞችም ከርሱ የኾነን መልካም ጸጋ ለመስጠት (ይህን አደረገ)፡፡ አላህ ሰሚ ዐዋቂ ነውና፡፡
18
ይህ (ዕውነት ነው)፡፡ አላህም የከሓዲዎችን ተንኮል አድካሚ ነው፡፡
19
ፍትሕን (ፍርድን) ብትጠይቁ ፍትሑ በእርግጥ መጥቶላችኋል፡፡ (ክህደትንና መዋጋትን) ብትከለከሉም እርሱ ለእናንተ የተሻለ ነው፡፡ (ወደ መጋደል) ብትመለሱም እንመለሳለን፡፡ ሰራዊታችሁም ብትበዛም እንኳ ከናንተ ምንም አትጠቅማችሁም፡፡ አላህም ከምእምናን ጋር ነው፡፡
20
እናንተ ያመናችሁ ሆይ! አላህንና መልክተኛውን ታዘዙ፡፡ እናንተም የምትሰሙ ስትኾኑ ከርሱ አትሽሹ፡፡
21
እንደነዚያም እነሱ የማይሰሙ ሲኾኑ ሰማን እንዳሉት አትሁኑ፡፡
22
ከተንቀሳቃሾች ሁሉ አላህ ዘንድ መጥፎ ተንኮለኞች እነዚያ የማያውቁት፣ ደንቆሮዎቹ፣ ዲዳዎቹ ናቸው፡፡
23
በውስጣቸውም ደግ መኖሩን አላህ ባወቀ ኖሮ (የመረዳትን መስማት) ባሰማቸው ነበር፡፡ (ደግ የሌለባቸው መኾኑን ሲያውቅ) ባሰማቸውም ኖሮ እነሱ እውነትን የተው ኾነው በሸሹ ነበር፡፡
24
እናንተ ያመናችሁ ሆይ! (መልክተኛው) ሕያው ወደሚያደርጋችሁ እምነት በጠራችሁ ጊዜ ለአላህና ለመልክተኛው ታዘዙ፡፡ አላህም በሰውየውና በልቡ መካከል የሚጋርድ መኾኑን ወደርሱም የምትሰበሰቡ መኾናችሁን እወቁ፡፡
25
ከናንተም ውስጥ እነዚያን የበደሉትን ብቻ ለይታ የማትነካን ፈተና ተጠንቀቁ፡፡ አላህም ቅጣቱ ብርቱ መኾኑን እወቁ፡፡
26
እናንተም በምድር ላይ የተናቃችሁ ጥቂቶች ኾናችሁ ሳላችሁ ሰዎች ሊነጥቁዋችሁ የምትፈሩ ስትኾኑ ያስጠጋችሁን በእርዳታውም ያበረታችሁን ከመልካሞች ሲሳዮችም ታመሰግኑ ዘንድ የሰጣችሁን አስታውሱ፡፡
27
እናንተ ያመናችሁ ሆይ! አላህንና መልክተኛውን አትክዱ፡፡ አደራዎቻችሁንም እናንተ እያወቃችሁ አትክዱ፡፡
28
ገንዘቦቻችሁና ልጆቻችሁም ፈተና ብቻ መኾናቸውንና አላህም እሱ ዘንድ ታላቅ ምንዳ ያለው መኾኑን እወቁ፡፡
29
እናንተ ያመናችሁ ሆይ! አላህን ብትፈሩ የእውነት መለያን ብርሃን ያደርግላችኋል፡፡ ክፉ ሥራዎቻችሁንም ከእናንተ ላይ ያብስላችኋል፡፡ ለእናንተም ይምራችኋል፡፡ አላህም የታላቅ ችሮታ ባለቤት ነው፡፡
30
እነዚያም የካዱት ሊያስሩህ ወይም ሊገድሉህ ወይም (ከመካ) ሊያወጡህ ባንተ ላይ በመከሩብህ ጊዜ (አስታውስ)፡፡ ይመክራሉም አላህም ተንኮላቸውን ይመልስባቸዋል፡፡ አላህም ከመካሪዎቹ ሁሉ በላይ ነው፡፡
Sonraki 30 ayet →