1
ምስጋና ለዚያ ሰማያትንና ምድርን ለፈጠረው ጨለማዎችንና ብርሃንንም ላደረገው ለአላህ የተገባ ነው፡፡ ከዚያም እነዚያ የካዱት (ጣዖታትን በጌታቸው) ያስተካክላሉ፡፡
2
እርሱ ያ ከጭቃ የፈጠራችሁ ከዚያም (የሞት) ጊዜን የወሰነ ነው፡፡ እርሱም ዘንድ (ለትንሣኤ) የተወሰነ ጊዜ አልለ፡፡ ከዚያም እናንተ (በመቀስቀሳችሁ) ትጠራጠራላችሁ፡፡
3
እርሱም ያ በሰማያትና በምድር (ሊግገዙት የሚገባው) አላህ ነው፡፡ ምስጢራችሁን ግልጻችሁንም ያውቃል፡፡ የምትሠሩትንም ሁሉ ያውቃል፡፡
4
ከጌታቸውም አንቀጾች አንዲትም አንቀጽ አትመጣቸውም ከርሷ የሚሸሹ ቢኾኑ እንጅ፡፡
5
በእውነቱም (ቁርኣን) በመጣላቸው ጊዜ በእርግጥ አስተባበሉ፡፡ በእርሱም ይሳለቁበት የነበሩት ነገር ዜናዎች (ቅጣት) በእርግጥ ይመጣባቸዋል፡፡
6
ከበፊታቸው ከክፍለ ዘመናት ሕዝቦች ብዙዎችን ማጥፋታችንን አላዩምን ለእናንተ ያላስመቸነውን (ለእነርሱ) በምድር ውስጥ አስመቸናቸው፡፡ በእነርሱም ላይ ዝናምን የተከታተለ ሲኾን ላክን፡፡ ወንዞችንም በሥራቸው እንዲፈሱ አደረግን፡፡ በኃጢአቶቻቸውም አጠፋናቸው፡፡ ከኋላቸውም ሌሎችን የክፍለ ዘመን ሰዎች አስገኘን፡፡
7
ባንተም ላይ በወረቀት የተጻፈን መጽሐፍ ባወረድንና በእጆቻቸው በነኩት ኖሮ እነዚያ የካዱት ሰዎች «ይህ ግልጽ ድግምት እንጅ ሌላ አይደለም» ባሉ ነበር፡፡
8
«በእርሱም (በሙሐመድ) ላይ መልአክ አይወረድለትም ኖሮአልን» አሉ፡፡ መልአክን ባወረድንም ኖሮ (ባያምኑ በጥፋታቸው) ነገሩ በተፈረደ ነበር፡፡ ከዚያም አይቆዩም ነበር፡፡
9
(መልክተኛውን) መልአክም ባደረግነው ኖሮ ወንድ (በሰው ምስል) ባደረግነው ነበር፡፡ በእነርሱም ላይ የሚያመሳስሉትን ነገር ባመሳሰልንባቸው ነበር፡፡
10
ካንተ በፊትም በመልክተኞች በእርግጥ ተላግጧል፡፡ በእነዚያም ከእነሱ ባላገጡት ላይ በእርሱ ያላግጡ የነበሩት ነገር (ቅጣት) ወረደባቸው፡፡
11
«በምድር ላይ ኺዱ የአስተባባዮችም መጨረሻ እንዴት እንደነበረ ተመልከቱ» በላቸው፡፡
12
«በሰማያትና በምድር ያለው ሁሉ የማን ነው» በላቸው፡፡ (ሌላ መልስ የለምና) «የአላህ ነው» በል፡፡ «በነፍሱ ላይ እዝነትን ጻፈ፡፡ በትንሣኤ ቀን በእርሱ ጥርጥር የሌለበት ሲኾን በእርግጥ ይሰበስባችኋል፡፡ እነዚያ ነፍሶቻቸውን ያከሰሩ ናቸው፤ እነርሱም አያምኑም፡፡
13
በሌሊትና በቀንም ጸጥ ያለው ሁሉ የርሱ ብቻ ነው፡፡ እርሱም ሰሚው ዐዋቂ ነው፡፡»
14
«ሰማያትንና ምድርን ፈጣሪ ከኾነው አላህ እርሱ የሚመግብ የማይመገብም ሲኾን ሌላን አምላክ እይዛለሁን» በላቸው፡፡ «እኔ መጀመሪያ ትእዛዝን ከተቀበለ ሰው ልኾን ታዘዝኩ፡፡ ከአጋሪዎችም ፈጽሞ አትኹን (ተብያለሁ)» በላቸው፡፡
15
«እኔ በጌታዬ ባምጽ የታላቁን ቀን ቅጣት እፈራለሁ» በላቸው፡፡
16
በዚያ ቀን ከእርሱ ላይ (ቅጣት) የሚመለስለት ሰው (አላህ) በእርግጥ አዘነለት፡፡ ይህም ግልጽ ማግኘት ነው፡፡
17
አላህም በጉዳት ቢነካህ ለእርሱ (ለጉዳቱ) ከእርሱ በቀር ሌላ አስወጋጅ የለም፡፡ በበጎም ነገር ቢነካህ እርሱ በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ ነው፡፡
18
እርሱም ከባሮቹ በላይ ሲኾን አሸናፊ ነው፡፡ እርሱም ጥበበኛው ውስጥ ዐዋቂው ነው፡፡
19
«በምስክርነት ከነገሩ ሁሉ ይበልጥ ታላቅ ማነው» በላቸው፡፡ (ሌላ መልስ የለምና) «አላህ ነው፡፡ በእኔና በእናንተ መካከል መስካሪ ነው፡፡ ይህም ቁርኣን እናንተንና የደረሰውን ሰው ሁሉ በርሱ ላስፈራራበት ወደኔ ተወረደ፡፡ ከአላህ ጋር ሌሎች አማልክት መኖራቸውን እናንተ ትመሰክራላችሁን» በላቸው፡፡ «እኔ አልመሰክርም» በላቸው፡፡ «እርሱ አንድ አምላክ ብቻ ነው፡፡ እኔም ከምታጋሩት ነገር ንጹሕ ነኝ» በላቸው፡፡
20
እነዚያ መጽሐፍን የሰጠናቸው ልጆቻቸውን እንደሚያውቁ (ሙሐመድን) ያውቁታል፡፡ እነዚያ ከእነርሱ ውስጥ ነፍሶቻቸውን ያከሰሩት እነርሱ አያምኑም፡፡
21
በአላህም ላይ ውሸትን ከቀጣጠፈ ወይም በአንቀጾቹ ካስተባበለ ሰው ይበልጥ በደለኛ ማነው እነሆ በደለኞች አይድኑም፡፡
22
ሁላቸውንም የምንሰበስብበትንና ከዚያም ለእነዚያ (ጣዖታትን) ለአጋሩት እነዚያ (ለአላህ) ተጋሪዎች ናቸው ብላችሁ ታስቧቸው የነበራችሁት ተጋሪዎቻችሁ የት ናቸው የምንልበትን ቀን (አስታውስ)፡፡
23
ከዚያም መልሳቸው «በጌታችን በአላህ ይኹንብን አጋሪዎች አልነበርንም» ማለት እንጅ ሌላ አትኾንም፡፡
24
በነፍሳቸው ላይ እንዴት እንደ ዋሹና ይቀጣጥፉት የነበሩት ነገር ከእነሱ እንዴት እንደ ተሰወረ ተመልከት፡፡
25
ከእነርሱም ወደ አንተ የሚያዳምጥ ሰው አልለ፡፡ በልቦቻቸውም ላይ እንዳያውቁት ሺፋኖችን በጆሮዎቻቸውም ላይ ድንቁርናን አደረግን፡፡ ተዓምርንም ሁሉ ቢያዩ በርሷ አያምኑም፡፡ በመጡህም ጊዜ የሚከራከሩህ ሲኾኑ እነዚያ የካዱት «ይህ (ቁርኣን) የቀድሞዎቹ ሰዎች ጽሑፍ ተረቶች እንጅ ሌላ አይደለም» ይላሉ፡፡
26
እነርሱም (ሰዎችን) ከእርሱ ይከለክላሉ፡፡ ከእርሱም ይርቃሉ፡፡ ነፍሶቻቸውንም እንጂ ሌላን አያጠፉም፤ ግን አያውቁም፡፡
27
በእሳትም ላይ በተቆሙ ጊዜ ምነው (ወደ ምድረ ዓለም) በተመለስን በጌታችንም አንቀጾች ባላስተባበልን ከምእምናንም በኾንን ዋ ምኞታችን! ባሉ ጊዜ ብታይ ኖሮ (የሚያሰደነግጥን ነገር ባየህ ነበር)፡፡
28
ይልቁንም ከዚህ በፊት ይደብቁት የነበሩት ሁሉ ለእነርሱ ተገለጸ፡፡ (ወደምድረ ዓለም) በተመለሱም ኖሮ ከእርሱ ወደ ተከለከሉት ነገር በተመለሱ ነበር፡፡ እነሱም በእርግጥ ውሸታሞች ናቸው፡፡
29
እርሷም (ሕይወት) «የቅርቢቱ ሕይወታችን እንጅ ሌላ አይደለችም እኛም ተቀስቀቃሾች አይደለንም» አሉ፡፡
30
በጌታቸውም ላይ (ለምርመራ) በተቆሙ ጊዜ ብታይ ኖሮ (አስደንጋጭን ነገር ባየህ ነበር)፡፡ «ይህ እውነት አይደለምን» ይላቸዋል፡፡ «በጌታችን ይኹንብን እውነት ነው» ይላሉ፡፡ «ትክዱት በነበራችሁት ምክንያት ቅጣቱን ቅመሱ» ይላቸዋል፡፡
Sonraki 30 ayet →