1
እናንተ ያመናችሁ ሆይ! በቃል ኪዳኖች ሙሉ፡፡ በእናንተ ላይ የሚነበበው ብቻ ሲቀር፡፡ የግመል፣ የከብት፣ የበግና የፍየል እንስሳዎች እናንተ በሐጅ ሥራ ላይ ኾናችሁ ማደንን የተፈቀደ ሳታደረጉ ለእናንተ ተፈቀዱ፡፡ አላህ የሚሻውን ይፈርዳል፡፡
2
እናንተ ያመናችሁ ሆይ! የአላህ (ክልክል ያደረጋቸውን) ምልክቶች የተፈቀዱ አታድርጉ፡፡ የተከበረውንም ወር በመጋደል አትድፈሩ፡፡ ወደ መካ የሚነዱትን መስዋዕትና የሚታበቱባቸውንም ገመዶች ከጌታቸው ችሮታንና ውዴታን ፈልገው ወደ ተከበረው ቤት አሳቢዎችንም ሰዎች (አትንኩ)፡፡ ከሐጅም ሥራ በወጣችሁ ጊዜ ዐድኑ፡፡ ከተከበረው መስጊድ ስለከለከሉዋችሁ ሰዎችን መጥላትም (በነሱ ላይ) ወሰን እንድታልፉ አይገፋፋችሁ፡፡ በበጎ ነገርና አላህን በመፍራትም ተረዳዱ፡፡ ግን በኃጢአትና ወሰንን በማለፍ አትረዳዱ፡፡ አላህንም ፍሩ፡፡ አላህ ቅጣተ ብርቱ ነውና፡፡
3
በክት፣ ፈሳሽ ደምም፣ የእሪያ (አሣማ) ሥጋም፣ በርሱ ከአላህ (ስም) ሌላ የተነሳበትም፣ የታነቀችም፣ ተደብድባ የተገደለችም፣ ተንከባላ የሞተችም፣ በቀንድ ተውግታ የሞተችም፣ ከርሷ አውሬ የበላላትም (ከእነዚህ በሕይወት ደርሳችሁ) ያረዳችሁት ብቻ ሲቀር ለጣዖታትም የታረደው በአዝላምም ዕድልን መፈለጋችሁ በእናንተ ላይ እርም ተደረገ፡፡ ይህ ድርጊት አመጽ ነው፡፡ ዛሬ እነዚያ የካዱት ከሃይማኖታችሁ ተስፋ ቆረጡ፡፡ ስለዚህ አትፍሩዋቸው፡፡ ፍሩኝም፡፡ ዛሬ ሃይማኖታችሁን ለናንተ ሞላሁላችሁ፡፡ ጸጋዬንም በናንተ ላይ ፈጸምኩ፡፡ ለእናንተም ኢስላምን ከሃይማኖት በኩል ወደድኩ፡፡ በረኃብ ወቅት ወደ ኃጢአት ያዘነበለ ሳይሆን (እርም የኾኑትን ለመብላት) የተገደደ ሰውም (ይብላ)፡፡ አላህ መሓሪ አዛኝ ነውና፡፡
4
ለእነርሱ ምን እንደተፈቀደላቸው ይጠይቁሃል፡፡ በላቸው፡- «ለእናንተ መልካሞች ሁሉና እነዚያም ከአዳኞች አሰልጣኞች ኾናችሁ ያስተማራችኋቸው (ያደኑት) ተፈቀደላችሁ፡፡ አላህ ከአስተማራችሁ ዕውቀት ታስተምሯቸዋላችሁ፡፡ ለእናንተም ከያዙላችሁ ነገር ብሉ፡፡ በርሱም ላይ የአላህን ስም አውሱ፡፡ አላህንም ፍሩ አላህ ምርመራው ፈጣን ነውና፡፡»
5
ዛሬ መልካሞች ሁሉ ለናንተ ተፈቀዱ፡፡ የእነዚያም መጽሐፍን የተሰጡት ሰዎች ምግብ (ያረዱት) ለእናንተ የተፈቀደ ነው፡፡ ምግባችሁም ለነሱ የተፈቀደ ነው፡፡ ከምእመናት ጥብቆቹም ከእነዚያ ከእናንተ በፊት መጽሐፍን ከተሰጡት ሴቶች ጥብቆቹም፤ ዘማዊዎችና (ዝሙተኞች) የምስጢር ወዳጅ ያዢዎች ሳትኾኑ ጥብቆች ኾናችሁ መህሮቻቸውን በሰጣችኋቸው ጊዜ (ልታገቡዋቸው የተፈቀዱ ናቸው)፡፡ ከእምነትም የሚመለስ ሰው በእርግጥ ሥራው ተበላሸ፡፡ በመጨረሻም ቀን እርሱ ከከሳሪዎቹ ነው፡፡
6
እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ወደ ሶላት በቆማችሁ (ለመቆም ባሰባችሁ) ጊዜ ፊቶቻችሁን፣ እጆቻችሁንም እስከ ክርኖች እጠቡ፡፡ ራሶቻችሁንም (በውሃ) አብሱ፡፡ እግሮቻችሁንም እስከ ቁርጭምጭሚቶች (እጠቡ)፡፡ (ሴት ጋር በመገናኘት ወይም በሌላ ምክንያት «ጀናባ») ብትኾኑ (ገላችሁን) ታጠቡ፡፡ በሽተኞች ወይም በጉዞ ላይ ብትኾኑም ወይም ከእናንተ አንዳችሁ ከዓይነ ምድር ቢመጣ ወይም ሴቶችን ብትነካኩና ውሃን ባታገኙ ንጹሕን የምድር ገጽ አስቡ ፡፡ ከሱም ፊቶቻችሁንና እጆቻችሁን አብሱ፡፡ አላህ በእናንተ ላይ ምንም ችግር ሊያደርግ አይሻም፡፡ ግን ታመሰግኑ ዘንድ ሊያጠራችሁና ጸጋውን በእናንተ ላይ ሊሞላ ይሻል፡፡
7
በእናንተም ላይ (የለገሰውን) የአላህን ጸጋ ያንንም ሰምተናል ታዘናልም ባላችሁ ጊዜ በርሱ ያጠበቀባችሁን ቃል ኪዳኑን አስታውሱ፡፡ አላህንም ፍሩ፡፡ አላህ በደረቶች ውስጥ ያለውን ሁሉ ዐዋቂ ነውና፡፡
8
እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ለአላህ ቀጥተኞች በትክክል መስካሪዎች ኹኑ፡፡ ሕዝቦችንም መጥላት ባለማስተካከል ላይ አይገፋፋችሁ፡፡ አስተካክሉ፡፡ እርሱ (ማስተካከል) ለአላህ ፍራቻ በጣም የቀረበ ነው፡፡ አላህንም ፍሩ፡፡ አላህ በምትሠሩት ሁሉ ውስጠ ዐዋቂ ነው፡፡
9
እነዚያንም ያመኑትንና በጎ ሥራዎችን የሠሩትን አላህ (ገነትን) ተስፋ አደረገላቸው፡፡ ለእነርሱ ምሕረትና ታላቅ ምንዳ አላቸው፡፡
10
እነዚያም የካዱና በተአምራቶቻችን ያስተባበሉ እነዚያ የእሳት ጓዶች ናቸው፡፡
11
እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ሕዝቦች እጆቻቸውን ወደ እናንተ ሊዘረጉ ባሰቡና እጆቻቸውን ከእናንተ ላይ በከለከላችሁ ጊዜ በናንተ ላይ (የዋለላችሁን) የአላህን ጸጋ አስታውሱ፡፡ አላህንም ፍሩ፡፡ ምእመናንም በአላህ ላይ ይመኩ፡፡
12
አላህም የእስራኤልን ልጆች የጠበቀ ቃል ኪዳን በእርግጥ ያዘባቸው፡፡ ከነርሱም ዐስራ ሁለትን አለቆች አስነሳን፡፡ አላህም አላቸው፤ «እኔ ከናንተ ጋር ነኝ፤ ሶላትን ብታስተካክሉ ግዴታ ምጽዋትንም ብትሰጡ በመልክተኞቼም ብታምኑ ብትረዱዋቸውም ለአላህም መልካም ብድርን ብታበድሩ ኀጢአቶቻችሁን ከናንተ በእርግጥ አብሳለሁ፡፡ ከሥሮቻቸው ወንዞች የሚፈሱባቸውን ገነቶችም በእርግጥ አገባችኋለሁ፡፡ ከዚህም በኋላ ከእናንተ የካደ ሰው ቀጥተኛውን መንገድ በእርግጥ ተሳሳተ፡፡»
13
ቃል ኪዳናቸውንም በማፍረሳቸው ረገምናቸው፡፡ ልቦቻቸውንም ደረቆች አደረግን፡፡ ቃላትን ከቦታዎቻቸው ይለውጣሉ፡፡ በርሱም ከታዘዙበት ነገር ፈንታን ተው፡፡ ከእነሱም ጥቂቶች ሲቀሩ ከነርሱ የኾነን ክዳት የምታውቅባቸው ከመኾን አትወገድም፡፡ ከእነርሱም ይቅርታ አድርግ እለፋቸውም፡፡ አላህ መልካም ሠሪዎችን ይወዳልና፡፡
14
ከእነዚያም እኛ ክርስቲያኖች ነን ካሉት የጠበቀ ቃል ኪዳናቸውን ያዝን፡፡ በእርሱም ከታዘዙበት ነገር ፈንታን ተውት፡፡ ስለዚህ እስከ ትንሣኤ ቀን ድረስ በመካከላቸው ጠብንና ጥላቻን ጣልንባቸው፡፡ አላህም ይሠሩት የነበሩትን ሁሉ በእርግጥ ይነግራቸዋል፡፡
15
የመጽሐፉ ባለቤቶች ሆይ! ከመጽሐፉ ትሸሽጉት ከነበራችሁት ነገር ብዙውን ለእናንተ የሚገልጽ ከብዙውም የሚተው ሲኾን መልክተኛችን (ሙሐመድ) በእርግጥ መጣላችሁ፡፡ ከአላህ ዘንድ ብርሃንና ገላጭ መጽሐፍ በእርግጥ መጣላችሁ፡፡
16
አላህ ውዴታውን የተከተሉትን ሰዎች የሰላምን መንገዶች በእርሱ ይመራቸዋል፡፡ በፈቃዱም ከጨለማዎች ወደ ብርሃን ያወጣቸዋል፡፡ ወደ ቀጥተኛም መንገድ ይመራቸዋል፡፡
17
እነዚያ አላህ እርሱ የመርየም ልጅ አልመሲሕ ነው ያሉ በእርግጥ ካዱ፡፡ የመርየምን ልጅ አልመሲሕን እናቱንም በምድር ያለንም ሁሉ ለማጥፋት ቢሻ ከአላህ ማዳንን የሚችል ማነው በላቸው፡፡ የሰማያትና የምድር የመካከላቸውም ንግሥና የአላህ ብቻ ነው፡፡ የሚሻውን ይፈጥራል፡፡ አላህም በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ ነው፡፡
18
አይሁዶችና ክርስቲያኖችም «እኛ የአላህ ልጆችና ወዳጆቹ ነን» አሉ፡፡ «ታዲያ በኃጢአቶቻችሁ ለምን ያሰቃያችኋል አይደላችሁም እናንተ ከፈጠራቸው ሰዎች ናችሁ» በላቸው፡፡ ለሚሻው ሰው ይምራል፡፡ የሚሻውንም ሰው ይቀጣል፡፡ የሰማያትና የምድርም በመካከላቸውም ያለው ሁሉ ንግሥና የአላህ ብቻ ነው፡፡ መመለሻም ወደርሱ ብቻ ነው፡፡
19
እናንተ የመጽሐፉ ሰዎች ሆይ! «አብሳሪና አስፈራሪ አልመጣልንም» እንዳትሉ ከመልክተኞች በመቋረጥ ጊዜ ላይ ሲኾን (ሕጋችንን) የሚያብራራ ኾኖ መልክተኛችን በእርግጥ መጣላችሁ፡፡ አብሳሪና አስፈራሪም በእርግጥ መጣላችሁ፡፡ አላህም በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ ነው፡፡
20
ሙሳም ለሕዝቦቹ ባለ ጊዜ (አስታውስ)፡- «ሕዝቦቼ ሆይ የአላህን ጸጋ በውስጣችሁ ነቢያትን ባደረገና ነገሥታትንም ባደረጋችሁ ከዓለማትም ለአንድም ያልሰጠውን ችሮታ በሰጣችሁ ጊዜ በእናንተ ላይ (ያደረገውን ጸጋ) አስታውሱ፡፡»
21
«ሕዝቦቼ ሆይ! ያችን አላህ ለእናንተ ያደረጋትን የተቀደሰችውን መሬት ግቡ፡፡ ወደ ኋላችሁም አትመለሱ፡፡ ከሳሪዎች ኾናችሁ ትመለሳላችሁና፡፡»
22
«ሙሳ ሆይ! በርስዋ ውስጥ ኀያላን ሕዝቦች አሉ፡፡ ከርስዋም እስከሚወጡ ድረስ እኛ ፈጽሞ አንገባትም፡፡ ከርስዋም ቢወጡ እኛ ገቢዎች ነን» አሉ፡፡
23
ከእነዚያ (አላህን) ከሚፈሩትና አላህ በእነርሱ ላይ ከለገሰላቸው የኾኑ ሁለት ሰዎች «በእነርሱ (በኀያሎቹ) ላይ በሩን ግቡ፡፡ በገባችሁትም ጊዜ እናንተ አሸናፊዎች ናችሁ፡፡ ምእመናንም እንደኾናችሁ በአላህ ላይ ተመኩ» አሉ፡፡
24
«ሙሳ ሆይ! በውስጧ እስካሉ ድረስ እኛ ፈጽሞ ምን ጊዜም አንገባትም፡፡ ስለዚህ ኺድ አንተና ጌታህ ተጋደሉም እኛ እዚህ ተቀማጮች ነን» አሉ፡፡
25
«ጌታዬ ሆይ እኔ ራሴንና ወንድሜን በቀር (ላስገድድ) አልችልም፡፡ በእኛና በአመጸኞቹም ሕዝቦች መካከል ለይ» አለ፡፡
26
እርስዋም (የተቀደሰችው መሬት) በእነርሱ ላይ አርባ ዓመት እርም ናት፡፡ በምድረ በዳ ይንከራተታሉ፡፡ «በአመጸኞችም ሕዝቦች ላይ አትዘን» አለው፡፡
27
በነርሱም ላይ የአደምን ሁለት ልጆች ወሬ ቁርባንን ባቀረቡና (አላህ) ከአንደኛቸው ተቀብሎ ከሌላው ባልተቀበለ ጊዜ (የኾነውን) በእውነት አንብብላቸው፡፡ «በእርግጥ እገድልሃለሁ» አለው፡፡ (ተገዳዩ) «አላህ የሚቀበለው እኮ ከጥንቁቆቹ ብቻ ነው» አለ፡፡
28
«ልትገድለኝ እጅህን ወደኔ ብትዘረጋ እኔ ልገድልህ እጄን ወዳንተ የምዘረጋ አይደለሁም፡፡ እኔ የዓለማትን ጌታ አላህን እፈራለሁና» አለ፡፡
29
«እኔ በኃጢአቴና በኃጢአትህ ልትመለስና ከእሳት ጓዶች ልትኾን እሻለሁ፤ ይኽም የበደለኞች ቅጣት ነው» (አለ)፡፡
30
ነፍሱም ወንድሙን መግደልን ለርሱ ሸለመችለት፤(አነሳሳችው፤)፡፡ ገደለውም፡፡ ከከሳሪዎቹም ኾነ፡፡
Sonraki 30 ayet →