1
እናንተ ሰዎች ሆይ! ያንን ከአንዲት ነፍስ (ከአዳም) የፈጠራችሁን ከእርስዋም መቀናጆዋን (ሔዋንን) የፈጠረውን ከእነርሱም ብዙ ወንዶችንና ሴቶች የበተነውን ጌታችሁን ፍሩ፡፡ ያንንም በርሱ የምትጠያየቁበትን አላህንና ዝምድናዎችንም (ከመቁረጥ) ተጠንቀቁ፡፡ አላህ በእናንተ ላይ ተጠባባቂ ነውና፡፡
2
የቲሞችንም ገንዘቦቻቸውን ስጡ፡፡ መጥፎውንም በመልካሙ አትለውጡ፡፡ ገንዘቦቻቸውንም ወደ ገንዘቦቻችሁ (በመቀላቀል) አትብሉ እርሱ ታላቅ ኃጢአት ነውና፡፡
3
በየቲሞችም (ማግባት) አለማስተካከላችሁን ብትፈሩ (ዝሙትንና ከተወሰነላችሁ በላይ ማግባትንም ፍሩ)፡፡ ከሴቶች ለእናንተ የተዋበላችሁን ሁለት ሁለት ሦስት ሦስትም አራት አራትም አግቡ፡፡ አለማስተካከልንም ብትፈሩ አንዲትን ብቻ ወይም እጆቻችሁ ንብረት ያደረጉትን ያዙ፡፡ ይህ ወደ አለመበደል በጣም የቀረበ ነው፡፡
4
ሴቶችንም መህሮቻቸውን በደስታ ስጡ፡፡ ለእናንተም ከእርሱ አንዳችን ነገር ነፍሶቻቸው ቢለግሱ መልካም ምስጉን ሲኾን ብሉት፡፡
5
ቂሎችንም ያችን አላህ ለእናንተ መተዳደሪያ ያደረጋትን ገንዘቦቻችውን (የያዛችሁላቸውን) አትስጡዋቸው፡፡ ከርሷም መግቡዋቸው አልብሱዋቸውም፡፡ ለእነሱም መልካምን ንግግር ተናገሩ፡፡
6
የቲሞችንም ጋብቻን እስከደረሱ ጊዜ ድረስ ፈትኑዋቸው፡፡ ከእነርሱም ቅንነትን ብታውቁ ገንዘቦቻቸውን ወደ እነርሱ ስጡ፡፡ በማባከንና ማደጋቸውንም በመሽቀዳደም አትብሏት፡፡ (ከዋቢዎች) ሀብታምም የኾነ ሰው ይከልከል፡፡ ድሃም የኾነ ሰው (ለድካሙ) በአግባብ ይብላ፡፡ ገንዘቦቻቸውንም ወደ እነርሱ በሰጣችሁ ጊዜ በእነርሱ ላይ አስመስክሩ፡፡ ተጠባባቂነትም በአላህ በቃ፡፡
7
ለወንዶች ወላጆችና የቅርብ ዘመዶች ከተዉት (ንብረት) ፋንታ (ድርሻ) አላቸው፡፡ ለሴቶችም ወላጆችና የቅርብ ዘመዶች ከተዉት ከእርሱ ካነሰው ወይም ከበዛው ፋንታ አላቸው፡፡ የተወሰነ ድርሻ (ተደርጓል)፡፡
8
ክፍያንም (ወራሽ ያልኾኑ) የዝምድና ባለቤቶችና የቲሞች፣ ምስኪኖችም በተገኙበት ጊዜ ከእርሱ ዳርጓቸው፡፡ መልካምንም ንግግር ተናገሩዋቸው፡፡
9
እነዚያም ከኋላቸው ደካሞችን ዝርያዎች ቢተው ኖሮ በእነርሱ ላይ የሚፈሩ (በየቲሞች ላይ) ይጠንቀቁ፡፡ አላህንም ይፍሩ፡፡ (ለተናዛዡ) ትክክለኛንም ቃል ይናገሩ፡፡
10
እነዚያ የየቲሞችን ገንዘብ በመበደል የሚበሉ በሆዶቻቸው ውስጥ የሚበሉት እሳትን ብቻ ነው፡፡ እሳትንም በእርግጥ ይገባሉ፡፡
11
አላህ በልጆቻችሁ (ውርስ በሚከተለው) ያዛችኋል፡፡ ለወንዱ የሁለት ሴቶች ድርሻ ብጤ አለው፡፡ (ሁለት ወይም) ከሁለት በላይም የኾኑ ሴቶች ብቻ ቢኾኑ ለእነሱ (ሟቹ) ከተወው ረጀት (ድርሻ) ከሦስት ሁለት እጁ አላቸው፡፡ አንዲትም ብትኾን ለርሷ ግማሹ አላት፡፡ ለአባትና ለእናቱም ለእርሱ ልጅ እንዳለው ከሁለቱ ለያንዳንዱ ከስድስት አንድ አላቸው፡፡ ለእርሱም ልጅ ባይኖረውና ወላጆቹ ቢወርሱት ለእናቱ ሲሶው አላት፡፡ ለእርሱም ወንድሞችና እኅቶች ቢኖሩት ለናቱ ከስድስት አንድ አላት፡፡ (ይህም የተባለው) በርሷ ከተናዘዘባት ኑዛዜ ወይም ከዕዳ በኋላ ነው፡፡ አባቶቻችሁና ልጆቻችሁ ለእናንተ በመጥቀም ማንኛቸው ይበልጥ ቅርብ እንደኾኑ አታውቁም፡፡ (ይኽም) ከአላህ የተደነገገ ነው፤ አላህ ዐዋቂ ጥበበኛ ነውና፡፡
12
ለእናንተም ሚስቶቻችሁ ከተዉት ንብረት ለእነርሱ ልጅ ባይኖራቸው ግማሹ አላችሁ፡፡ ለእነሱም ልጅ ቢኖራቸው ከተዉት ሀብት ከአራት አንድ አላችሁ፡፡ (ይህም) በእርሷ ከሚናዘዙባት ኑዛዜ ወይም ከዕዳ በኋላ ነው፡፡ ለናንተም ልጅ ባይኖራችሁ ከተዋችሁት ንብረት ለእነርሱ (ለሚስቶች) ከአራት አንድ አላቸው፡፡ ለእናንተም ልጅ ቢኖራችሁ ከተዋችሁት ንብረት ለእነርሱ ከስምንት አንድ አላቸው (ይህም በርሷ ከምትናዘዙባት ኑዛዜ ወይም ከዕዳ በኋላ ነው፡፡) ወላጅም ልጅም የሌለው በጎን ወራሾች የሚወርስ ወንድ ወይም ሴት ቢገኝ ለእርሱም (ለሟቹ) ወንድም ወይም እኅት (ከእናቱ በኩል ብቻ የኾነ) ቢኖር ከሁለቱ ለያንዳንዳቸው ከስድስት አንድ አላቸው፡፡ ከዚህም (ከአንድ) የበዙ ቢኾኑ እነርሱ በሲሶው ተጋሪዎች ናቸው፡፡ (ይህም ወራሾችን) የማይጎዳ ኾኖ በእርሷ ከሚናዘዙባት ኑዛዜ ወይም ከዕዳ በኋላ ነው፡፡ ከአላህም የኾነን ኑዛዜ (ያዛችኋል)፡፡ አላህም ዐዋቂ ቻይ ነው፡፡
13
እነዚህ የአላህ ውሳኔዎች ናቸው፡፡ አላህንና መልክተኛውንም የሚታዘዙ ሰዎች ከሥሮቻቸው ወንዞች የሚፈሱባቸውን ገነቶች በውስጣቸው ዘውታሪዎች ሲኾኑ ያገባቸዋል፡፡ ይህም ትልቅ ዕድል ነው፡፡
14
አላህንና መልክተኛውንም የሚያምጽ ወሰኖቹንም የሚተላለፍ በውስጧ ዘውታሪ ሲኾን እሳትን ያገባዋል፡፡ ለርሱም አዋራጅ ቅጣት አለው፡፡
15
እነዚያም ከሴቶቻችሁ መጥፎን ሥራ (ዝሙትን) የሚሠሩ በእነርሱ ላይ ከናንተ አራትን (ወንዶች) አስመስክሩባቸው፡፡ ቢመሰክሩም ሞት እስከሚደርስባቸው ወይም አላህ ለእነርሱ መንገድን እስከሚያደርግ ድረስ በቤቶች ውሰጥ ያዙዋቸው (ጠብቁዋቸው)፡፡
16
እነዚያንም ከእናንተ ውስጥ (ዝሙትን) የሚሠሩዋትን አሰቃዩዋቸው፡፡ ቢጸጸቱና ሥራቸውንም ቢያሳምሩ ከእነርሱ ተገቱ (አታሰቃዩዋቸው)፡፡ አላህ ጸጸትን ተቀባይ አዛኝ ነውና፡፡
17
ጸጸትን መቀበል በአላህ ላይ የሚገባው ለእነዚያ ኀጢአትን በስህተት ለሚሠሩና ከዚያም ከቅርብ ጊዜ ለሚጸጸቱት ብቻ ነው፡፡ እነዚያንም አላህ በእነርሱ ላይ ጸጸትን ይቀበላል፡፡ አላህም ዐዋቂ ጥበበኛ ነው፡፡
18
ጸጸትንም መቀበል ለእነዚያ ኀጢአቶችን ለሚሠሩ አንዳቸውንም ሞት በመጣበት ጊዜ «እኔ አሁን ተጸጸትኩ» ለሚልና ለነዚያም እነርሱ ከሓዲዎች ኾነው ለሚሞቱ አይደለችም፡፡ እነዚያ ለእነሱ አሳማሚን ቅጣት አዘጋጅተናል፡፡
19
እናንተ ያመናችሁ ሰዎች ሆይ! ሴቶችን ያስገደዳችሁ ኾናችሁ ልትወርሱና ግልጽን መጥፎ ሥራ ካልሠሩ በስተቀር ከሰጣችኋቸው ከፊሉን ልትወስዱ ልታጉላሏቸውም ለእናንተ አይፈቀድም፡፡ በመልካምም ተኗኗሩዋቸው፡፡ ብትጠሉዋቸውም (ታገሱ)፡፡ አንዳችን ነገር ብትጠሉ አላህም በእርሱ ብዙ ደግ ነገርን ሊያደርግ ይቻላልና፡፡
20
በሚስትም ስፍራ ሚስትን ለመለወጥ ብትፈልጉ ለአንደኛይቱ (ለምትፈታው) ብዙን ገንዘብ የሰጣችኋት ስትኾኑ ከርሱ ምንንም አትውሰዱ፡፡ በመበደልና ግልጽ በኾነ ኀጢአት ትወስዱታላችሁን
21
ከፊላችሁ ወደ ከፊሉ በእርግጥ የደረሰ ሲኾንና ከእናንተ ላይም (ሴቶች) የጠበቀ ኪዳንን የያዙባችሁ ሲኾኑ እንዴት ትወስዱታላችሁ!
22
ከሴቶችም አባቶቻችሁ ያገቡዋቸውን አታግቡ፡፡ (ትቀጡበታላችሁ)፡፡ ያለፈው ሲቀር፡፡ እርሱ መጥፎና የተጠላ ሥራ ነውና፡፡ መንገድነቱም ከፋ!
23
እናቶቻችሁ፣ ሴት ልጆቻችሁም፣ እኅቶቻችሁም፣ አክስቶቻችሁም፣ የሹሜዎቻችሁም፣ የወንድም ሴቶች ልጆችም፣ የእኅት ሴቶች ልጆችም፣ እነዚያም ያጠቡዋችሁ እናቶቻችሁ፣ ከመጥባት የኾኑትም እኅቶቻችሁ፣ የሚስቶቻችሁም እናቶች፣ እነዚያም በጉያዎቻችሁ ያሉት የእነዚያ በእነርሱ የገባችሁባቸው ሚስቶቻችሁ ሴቶች ልጆች፣ (ልታገቧቸው) በእናንተ ላይ እርም ተደረጉባችሁ፡፡ በእነርሱም (በሚስቶቻችሁ) ያልገባችሁባቸው ብትኾኑ (በፈታችኋቸው ጊዜ ሴቶች ልጆቻቸውን ብታገቡ) በእናንተ ላይ ኀጢአት የለባችሁም፡፡ የእነዚያ ከጀርባዎቻችሁ የኾኑት ወንዶች ልጆቻችሁ ሚስቶችም በሁለት እኅትማማቾችም መካከል መሰብሰብ (እንደዚሁ እርም ነው)፡፡ ግን ከዚህ በፊት ያለፈው ሲቀር (እርሱንስ ተምራችኋል) አላህ መሓሪ አዛኝ ነውና፡፡
24
ከሴቶችም (በባል) ጥብቆቹ እጆቻቸሁ (በምርኮ) የያዙዋቸው ሲቀሩ በእናንተ ላይ እርም ናቸው፡፡ (ይህን) አላህ በናንተ ላይ ጻፈ፡፡ ከዚሃችሁም (ከተከለከሉት) ወዲያ ጥብቆች ኾናችሁ ዝሙተኞች ሳትኾኑ በገንዘቦቻችሁ ልትፈልጉ ለእናንተ ተፈቀደ፡፡ ከእነሱም በርሱ (በመገናኘት) የተጠቀማችሁባቸውን ሴቶች መህሮቻቸውን ግዴታ ሲኾን ስጧቸው፡፡ ከመወሰንም በኋላ በተዋደዳችሁበት ነገር በእናንተ ላይ ኀጢአት የለም፡፡ አላህ ዐዋቂ ጥበበኛ ነውና፡፡
25
ከናንተም ውስጥ ጥብቆች ምእምናት የኾኑትን ለማግባት ሀብትን ያልቻለ ሰው እጆቻችሁ ንብረት ካደረጓቸው ከምእምናት ወጣቶቻችሁ (ባሪያን ያግባ)፡፡ አላህም እምነታችሁን ዐዋቂ ነው፡፡ ከፊላችሁ ከከፊሉ (የተራባ) ነው፡፡ (ባሮችን) በጌቶቻቸውም ፈቃድ አግቡዋቸው፡፡ መህሮቻቸውንም በመልካም መንገድ ስጧቸው፡፡ ጥብቆች ኾነው ዝሙተኞች ያልኾኑ የስርቆሽ ወዳጆችንም ያልያዙ ሲኾኑ (አግቧቸው)፡፡ በማግባት በተጠበቁም ጊዜ መጥፎን ሥራ ቢሠሩ በእነርሱ ላይ ከቅጣት በነጻዎቹ ላይ ያለው ግማሽ አለባቸው፡፡ ይኸ (ባሪያን ማግባት) ከናንተ ዝሙትን ለፈራ ሰው ነው፡፡
26
አላህ (የሃይማኖታችሁን ሕግጋት) ሊያብራራላችሁ ከእናንተ በፊትም የነበሩትን ነቢያት ደንቦች ሊመራችሁ በእናንተም ላይ ጸጸትን ሊቀበል ይሻል፡፡ አላህም ዐዋቂ ጥበበኛ ነው፡፡
27
አላህም በእናንተ ላይ ጸጸትን ሊቀበል ይሻል፡፡ እነዚያም ፍላጎታቸውን የሚከተሉት (ከውነት) ትልቅን መዘንበል እንድትዘነበሉ ይፈልጋሉ፡፡
28
አላህ ከእናንተ ሊያቃልልላችሁ ይሻል፡፡ ሰውም ደካማ ኾኖ ተፈጠረ፡፡
29
እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ገንዘቦቻችሁን በመካከላችሁ ያለ አግባብ አትብሉ፡፡ ግን ከእናንተ በመዋደድ የኾነችውን ንግድ (ብሉ)፡፡ ነፍሶቻችሁንም አትግደሉ፡፡ አላህ ለእናንተ አዛኝ ነውና፡፡
30
ወሰን በማለፍና በመበደልም ይህንን የሠራ ሰው እሳትን እናገባዋለን፡፡ ይኸም በአላህ ላይ ገር ነው፡፡
Sonraki 30 ayet →