2
አላህ ከርሱ በስተቀር ሌላ አምላክ የለም፡፡ (እርሱ) ሕያው ሁሉን ነገር አስተናባሪ ነው፡፡
3
ከርሱ በፊት ያሉትን መጻሕፍት የሚያረጋግጥ ሲኾን መጽሐፉን (ቁርኣንን) ባንተ ላይ ከፋፍሎ በእውነት አወረደ፡፡ ተውራትንና ኢንጂልንም አውርዷል፡፡
4
(ከቁርኣን) በፊት ለሰዎች መሪ አድርጎ (አወረዳቸው)፡፡ ፉርቃንንም አወረደ፡፡ እነዚያ በአላህ ተዓምራቶች የካዱ ለእነርሱ ብርቱ ቅጣት አላቸው፡፡ አላህም አሸናፊ የመበቀል ባለቤት ነው፡፡
5
አላህ በምድርም በሰማይም ምንም ነገር በርሱ ላይ አይሰወርም፡፡
6
እርሱ ያ በማሕጸኖች ውስጥ እንደሚሻ አድርጎ የሚቀርጻችሁ ነው፡፡ ከእርሱ በስተቀር ሌላ አምላክ የለም፡፡ አሸናፊው ጥበበኛው ነው፡፡
7
እርሱ ያ በአንተ ላይ መጽሐፉን ያወረደ ነው፡፡ ከእርሱ (ከመጽሐፉ) ግልጽ የኾኑ አንቀጾች አልሉ፡፡ እነሱ የመጽሐፉ መሠረቶች ናቸው፡፡ ሌሎችም ተመሳሳዮች አልሉ፡፡ እነዚያማ በልቦቻቸው ውስጥ ጥመት ያለባቸው ሰዎች ማሳሳትን ለመፈለግና ትችቱን ለመፈለግ ከርሱ የተመሳሰለውን ይከታተላሉ፡፡ (ትክክለኛ) ትችቱንም አላህ ብቻ እንጅ ሌላ አያውቀውም፡፡ በዕውቀትም የጠለቁት «በርሱ አምነናል፤ ሁሉም ከጌታችን ዘንድ ነው» ይላሉ፡፡ የአእምሮ ባለቤቶችም እንጅ (ሌላው) አይገሰጽም፡፡
8
(እነሱም ይላሉ)፡- «ጌታችን ሆይ! ቅኑን መንገድ ከመራኸን በኋላ ልቦቻችንን አታዘምብልብን፡፡ ከአንተ ዘንድ የኾነን ችሮታም ለኛ ስጠን፡፡ አንተ በጣም ለጋስ ነህና፡፡»
9
«ጌታችን ሆይ! አንተ በርሱ (ለመምጣቱ) ጥርጥር የሌለበት በኾነ ቀን ሰውን ሁሉ ሰብሳቢ ነህ፡፡ ምንጊዜም አላህ ቀጠሮውን አያፈርስምና፡፡»
10
እነዚያ የካዱት ሰዎች ገንዘቦቻቸውና ልጆቻቸው ከአላህ (ቅጣት) ምንም አያስጥሉዋቸውም፡፡ እነዚያም እነርሱ የእሳት ማገዶዎች ናቸው፡፡
11
(ልማዳቸው ሁሉ) እንደፈርዖን ቤተሰብና እንደእነዚያ ከበፊታቸው እንደነበሩት ሕዝቦች ልማድ ነው፡፡ በአንቀጾቻችን አስተባበሉ፡፡ አላህም በኃጢአቶቻቸው ያዛቸው፡፡ አላህም ቅጣተብርቱ ነው፡፡
12
ለእነዚያ ለካዱት ሰዎች በላቸው፡- «በቅርብ ጊዜ ትሸነፉላችሁ፡፡ ወደ ገሀነምም ትሰበሰባላችሁ፡፡ ምንጣፊቱም ምን ትከፋ!»
13
(የበድር ቀን) በተጋጠሙት ሁለት ጭፍሮች ለናንተ በእርግጥ ተዓምር አልለ፡፡ አንደኛዋ ጭፍራ በአላህ መንገድ ትጋደላለች፡፡ ሌላይቱም ከሓዲ ናት፡፡ ከሓዲዎቹ (አማኞቹን) በዓይን አስተያየት እጥፋቸውን ኾነው ያዩዋቸዋል፡፡ አላህም በርዳታው የሚሻውን ሰው ያበረታል፡፡ በዚህ ውስጥ ለማስተዋል ባለቤቶች በእርግጥ መገሰጫ አለበት፡፡
14
ከሴቶች፣ ከወንዶች ልጆችም፣ ከወርቅና ከብር፣ ከተካመቹ ገንዘቦችም፣ ከተሰማሩ ፈረሶችም፣ ከግመል ከከብትና ከፍየልም፣ ከአዝመራም የኾኑ ፍላጎቶችን መውደድ ለሰዎች ተሸለመ፡፡ ይህ ሁሉ የቅርቢቱ ሕይወት መጠቀሚያ ነው፡፡ አላህም እርሱ ዘንድ መልካም መመለሻ (ገነት) አለ፡፡
15
«ከዚህ ሁሉ ነገር የሚበልጥን ልንገራችሁን» በላቸው፡፡ (እርሱም) «ለእነዚያ ለተጠነቀቁት ሰዎች በጌታቸው ዘንድ በሥራቸው ወንዞች የሚፈሱባቸው ገነቶች በውስጧ ሁልጊዜ ነዋሪዎች ሲኾኑ ንጹሕ የተደረጉ ሚስቶችም፣ ከአላህም የኾነ ውዴታ አላቸው፡፡ አላህም ባሮቹን ተመልካች ነው፡፡»
16
(እነርሱም) እነዚያ፡- «ጌታችን ሆይ! እኛ አመንን ኀጢአቶቻችንንም ለእኛ ማር፤ የእሳትንም ቅጣት ጠብቀን» የሚሉ ናቸው፡፡
17
ታጋሾች እውነተኞችም ታዛዦችም ለጋሶችና በሌሊት መጨረሻዎች ምሕረትን ለማኞች ናቸው፡፡
18
አላህ በማስተካከል የቆመ (አስተናባሪ) ሲኾን ከእርሱ በስተቀር ሌላ አምላክ የሌለ መኾኑን መሰከረ፡፡ መላእክቶችና የዕውቀት ባለቤቶችም (እንደዚሁ መሰከሩ)፡፡ ከእርሱ በስተቀር ሌላ አምላክ የለም፡፡ አሸናፊው ጥበበኛው ነው፡፡
19
አላህ ዘንድ (የተወደደ) ሃይማኖት ኢስላም ብቻ ነው፡፡ እነዚያም መጽሐፉን የተሰጡት ሰዎች በመካከላቸው ላለው ምቀኝነት ዕውቀቱ ከመጣላቸው በኋላ እንጅ አልተለያዩም፡፡ በአላህም አንቀጾች የሚክድ አላህ ምርመራው ፈጣን ነው፡፡
20
ቢከራከሩህም፡- «ፊቴን ለአላህ ሰጠሁ፤ የተከተሉኝም ሰዎች (እንደዚሁ ለአላህ ሰጡ)» በላቸው፡፡ ለእነዚያም መጽሐፍን ለተሰጡት ሰዎችና ለመሐይሞቹ፡- «ሰለማችሁን» በላቸው፡፡ ቢሰልሙም በእርግጥ ተመሩ፡፡ እምቢ ቢሉም በአንተ ላይ ያለብህ ማድረስ ብቻ ነው፡፡ አላህም ባሮቹን ተመልካች ነው፡፡
21
እነዚያ በአላህ አንቀጾች የሚክዱ ነቢያትንም ያለ አግባብ የሚገድሉ ከሰዎችም ውስጥ እነዚያን በትክክለኛነት የሚያዙትን የሚገድሉ በአሳማሚ ቅጣት አብስራቸው፡፡
22
እነዚያ በቅርቢቱና በመጨረሻይቱ ዓለም ሥራዎቻቸው የተበላሹ ናቸው፡፡ ለእነርሱም ምንም ረዳቶች የሏቸውም፡፡
23
ወደ እነዚያ ከመጽሐፉ (ትምህርት) ዕድልን ወደ ተሰጡት ሰዎች አላየህምን ወደ አላህ መጽሐፍ በመካከላቸው ይፈርድ ዘንድ ይጠራሉ፡፡ ከዚያም ከእነሱ ገሚሶቹ እነርሱ (እውነቱን) የተዉ ኾነው ይሸሻሉ፡፡
24
ይኸ እነርሱ «እሳት የተቆጠሩ ቀኖችን እንጅ አትነካንም» በማለታቸው ነው፡፡ በሃይማኖታቸውም ይቀጣጥፉት የነበሩት ነገር አታለላቸው፡፡
25
በርሱ (መምጣት) ጥርጥር የሌለበት በኾነው ቀን በሰበሰብናቸውና ነፍስ ሁሉ የሠራችውን ሥራ በተሞላች ጊዜ እንዴት ይኾናሉ እነርሱም አይበደሉም፡፡
26
(ሙሐመድ ሆይ!) በል፡- «የንግስና ባለቤት የኾንክ አላህ ሆይ! ለምትሻው ሰው ንግሥናን ትሰጣለህ፡፡ ከምትሻውም ሰው ንግሥናን ትገፍፋለህ፡፡ የምትሻውንም ሰው ታልቃለህ፡፡ የምትሻውንም ሰው ታዋርዳለህ፡፡ መልካም ነገር ሁሉ በእጅህ (በችሎታህ) ነው፤ አንተ በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ ነህና፡፡»
27
ሌሊቱን በቀን ውስጥ ታስገባለህ፡፡ ቀኑንም በሌሊቱ ውስጥ ታስገባለህ፡፡ ሕያውንም ከሙት ውስጥ ታወጣለህ፡፡ ሙትንም ከሕያው ውስጥ ታወጣለህ፡፡ ለምትሻውም ሰው ያለግምት ትሰጣለህ፡፡
28
ምእምናን ከሓዲዎችን ከምእምናን ሌላ ረዳቶች አድርገው አይያዙ፡፡ ይኼንንም የሚሠራ ሰው ከአላህ (ሃይማኖት) በምንም ውስጥ አይደለም፡፡ ከእነርሱ መጥጠበቅን ብትጠበቁ እንጂ፡፡ አላህም ነፍሱን (ቁጣውን) ያስጠነቅቃችኋል፡፡ መመለሻም ወደ አላህ ብቻ ነው፡፡
29
«በደረቶቻችሁ ውስጥ ያለውን ነገር ብትደብቁ ወይም ብትገልፁት አላህ ያውቀዋል፡፡ በሰማያት ያለውንና በምድርም ያለውን ሁሉ ያውቃል፡፡ አላህም በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ ነው» (በል)፡፡
30
ነፍስ ሁሉ ከመልካም ነገር የሠራችውን የቀረበ ኾኖ የምታገኝበትን ቀን (አስታውስ)፡፡ ከመጥፎም የሠራችው በርስዋና በርሱ (በኀጢአትዋ) መካከል በጣም የሰፋ ርቀት ቢኖር ትመኛለች፡፡ አላህ ነፍሱን ያስጠነቅቃችኋል፡፡ አላህም ለባሮቹ ሩኅሩኅ ነው፡፡
Sonraki 30 ayet →