1
እናንተ ሰዎች ሆይ! ጌታችሁን ፍሩ የሰዓቲቱ እንቅጥቃጤ በጣም ከባድ ነገር ነውና፡፡
2
በምታዩዋት ቀን አጥቢ ሁሉ ከአጠባችው ልጅ ትፈዝዛለች፡፡ የእርግዝና ባለቤት የኾነችም ሁሉ እርጉዟን ትጨነግፋለች፡፡ ሰዎቹንም (በድንጋጤ ብርታት) የሰከሩ ኾነው ታያለህ፡፡ እነርሱም (ከመጠጥ) የሰከሩ አይደሉም፡፡ ግን የአላህ ቅጣት ብርቱ ነው፡፡
3
ከሰዎቹም ያለ ዕውቀት በአላህ ነገር የሚከራከር፤ ሞገደኛ ሰይጣንንም ሁሉ የሚከተል ሰው አልለ፡፡
4
እነሆ! የተከተለውን ሰው እርሱ ያጠመዋል፡፡ ወደ ነዳጅ እሳት ስቃይም ይመራዋል ማለት በርሱ ላይ ተጽፏል፡፡
5
እናንተ ሰዎች ሆይ! ከመቀስቀስ በመጠራጠር ውስጥ እንደ ሆናችሁ (አፈጣጠራችሁን ተመልከቱ)፡፡ እኛም ከዐፈር ፈጠርናችሁ፣ ከዚያም ከፍትወት ጠብታ፣ ከዚያም ከረጋ ደም፣ ከዚያም ከቁራጭ ሥጋ፣ ፍጥረትዋ ሙሉ ከሆነችና ሙሉ ካልሆነች (ችሎታችንን) ለናንተ ልንገልጽላችሁ ፈጠርናችሁ፡፡ የምንሻውንም እስከ ተወሰነ ጊዜ ድረስ በማሕፀን ውስጥ እናረጋዋለን፡፡ ከዚያም ሕፃን ሆናችሁ እናወጣችኋለን፡፡ ከዚያም ሙሉ ጥንካሪያችሁን ትደርሱ ዘንድ (እናሳድጋችኋለን)፡፡ ከእናንተም የሚሞት ሰው አልለ፡፡ ከእናንተም ከዕውቀት በኋላ ምንንም እንዳያውቅ ወደ ወራዳ ዕድሜ የሚመለስ ሰው አልለ፡፡ ምድርንም ደረቅ ሆና ታያታለህ፡፡ በእርሷም ላይ ውሃን ባወረድን ጊዜ ትላወሳለች፡፡ ትነፋፋለችም፡፡ ውበት ካለው ጎሳ ሁሉ ታበቅላለችም፡፡
6
ይህ አላህ እርሱ መኖሩ የተረጋገጠ፣ እርሱም ሙታንን ሕያው የሚያደርግ፣ እርሱም በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ በመሆኑ ነው፡፡
7
ሰዓቲቱም መጪ ፣ በእርሷ ፈጽሞ ጥርጣሬ የሌለባት በመሆኗ፣ አላህም በመቃብሮች ውስጥ ያለን ሁሉ የሚቀሰቅስ በመሆኑ ነው፡፡
8
ከሰዎችም ውስጥ ያለ ዕውቀት፣ ያለ ማስረጃም፣ ያለ አብራሪ መጽሐፍም በአላህ ነገር የሚከራከር ሰው አልለ፡፡
9
ጎኑን ያጠፈ ሆኖ ከአላህ መንገድ ሊያሳስት (ይከራከራል)፡፡ በቅርቢቱ ዓለም ለእርሱ ውርደት አልለው፡፡ በትንሳኤ ቀንም አቃጣይን ቅጣት እናቀምሰዋለን፡፡
10
ይህ እጆችህ ባስቀደሙት ኀጢአት አላህም ለባሮቹ ፈጽሞ በዳይ ባለመሆኑ ነው (ይባላል)፡፡
11
ከሰዎችም (ከሃይማኖት) በጫፍ ላይ ሆኖ አላህን የሚግገዛ ሰው አልለ፡፡ ታዲያ መልካም ነገር ቢያገኘው በእርሱ ይረጋል፡፡ መከራም ብታገኘው በፊቱ ላይ ይገለበጣል፡፡ የቅርቢቱን ዓለምም የመጨረሻይቱንም ከሰረ፡፡ ይህ እርሱ ግልጽ ከሳራ ነው፡፡
12
ከአላህ ሌላ የማይጎዳውንና የማይጠቅመውን ይግገዛል፡፡ ይህ እርሱ (ከእውነት) የራቀ ስህተት ነው፡፡
13
ያንን ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ የሚቀርብን ይግገዛል፡፡ ረዳቱ ምንኛ ከፋ!
14
አላህ እነዚያን ያመኑትንና መልካም ሥራዎችን የሠሩትን በሥሮቻቸው ወንዞች የሚፈሱባቸውን ገነቶች ያገባቸዋል፡፡ አላህ የሚሻውን ነገር በእርግጥ ይሠራል፡፡
15
አላህ (መልክተኛውን) በቅርቢቱም በመጨረሻይቱም ዓለም አይረዳውም ብሎ የሚያስብ ሰው ገመድን ወደ ሰማይ ይዘርጋ፡፡ ከዚያም (ትንፋሹ እስኪቆረጥ) ይታነቅ፡፡ ተንኮሉ የሚያስቆጨውን ነገር ያስወግድለት እንደሆነም ይመልከት፡፡
16
እንደዚሁም (ቁርኣንን) የተብራሩ አንቀጾች አድርገን አወረድነው፡፡ አላህም የሚሻውን ሰው ይመራል፡፡
17
እነዚያ ያመኑት፣ እነዚያም ይሁዳውያን የሆኑ፣ ሳቢያኖችም፣ ክርስቲያኖችም፣ መጁሶችም እነዚያም (ጣዖታትን በአላህ) ያጋሩ አላህ በትንሣኤ ቀን በመካከላቸው በፍርድ ይለያል፡፡ አላህ በነገሩ ሁሉ ላይ በእርግጥ ዐዋቂ ነውና፡፡
18
አላህ በሰማያት ያለው ሁሉ፣ በምድርም ያለው ሁሉ፣ ፀሐይና ጨረቃም፣ ከዋክብትም፣ ተራራዎችም፣ ዛፎችም፣ ተንቀሳቃሾችም ከሰዎች ብዙዎችም፣ ለርሱ የሚሰግዱለት መሆኑን አታውቁምን ብዙውም በርሱ ላይ ቅጣት ተረጋገጠበት፡፡ አላህ የሚያዋርደውም ሰው ለእርሱ ምንም አክባሪ የለውም፡፡ አላህ የሻውን ይሠራልና፡፡
19
እነዚህ በጌታቸው የተከራከሩ ሁለት ባላጋራዎች ናቸው፡፡ እነዚያም የካዱት ለእነርሱ የእሳት ልብሶች ተለክተውላቸዋል፡፡ ከራሶቻቸው በላይ የፈላ ውሃ ይምቧቧቸዋል፡፡
20
በሆዶቻቸው ውስጥ ያሉ ቆዳዎቻቸውም በእርሱ ይቀለጣሉ፡፡
21
ለእነሱም (መቅጫ) ከብረት የሆኑ መዶሻዎች አልሉ፡፡
22
ከጭንቀት ብርታት የተነሳ ከእርሷ ለመውጣት በፈለጉ ቁጥር ከእርሷ ውስጥ እንዲመለሱ ይደረጋሉ፡፡ «በጣም የሚያቃጥልንም ቅጣት ቅመሱ» (ይባላሉ)፡፡
23
አላህ እነዚያን ያመኑትንና መልካም ሥራዎችን የሠሩትን ሰዎች በሥሮቻቸው ወንዞች የሚፈስሱባቸውን ገነቶች ያገባቸዋል፡፡ በእርሷ ውስጥ ከወርቅ የሆኑን አንባሮችና ሉልን ይሸለማሉ፡፡ በእርሷ ውስጥ ልብሶቻቸውም ሐር ናቸው፡፡
24
ከንግግርም ወደ መልካሙ ተመሩ፡፡ ወደ ምስጉንም መንገድ ተመሩ፡፡
25
እነዚያ የካዱ ከአላህም መንገድና ከዚያም ለሰዎች በውስጡ ነዋሪ ለሆኑትም፣ ከሩቅ ለሚመጡትም እኩል ካደረግነው ከተከበረው መስጊድ (ሰዎችን) የሚከለክሉ (አሳማሚን ቅጣት እናቀምሳቸዋለን)፡፡ በእርሱም ውስጥ (ከትክክለኛ መንገድ) በመዘንበል በዳይ ሆኖ (ማንኛውንም ነገር) የሚፈልግ ሰው ከአሳማሚ ቅጣት እናቀምሰዋለን፡፡
26
ለኢብራሂምም የቤቱን (የካዕባን) ስፍራ መመለሻ ባደረግንለት ጊዜ «በእኔ ምንንም አታጋራ፣ ቤቴንም ለሚዞሩትና ለሚቆሙበት ለሚያጎነብሱትና በግንባራቸውም ለሚደፉት ንጹሕ አድርግላቸው» (ባልነው ጊዜ አስታውስ)፡፡
27
(አልነውም)፡- በሰዎችም ውስጥ በሐጅ ትዕዛዝ ጥራ፡፡ እግረኞች ከየሩቅ መንገድ በሚመጡ ከሲታ ግመሎችም ሁሉ ላይ ሆነው ይመጡሃልና፡፡
28
ለእነሱ የሆኑ ጥቅሞችን ይጣዱ ዘንድ በታወቁ ቀኖችም ውስጥ ከለማዳ እንስሳዎች በሰጣቸው ሲሳይ ላይ የአላህን ስም ያወሱ ዘንድ (ይመጡሃል)፡፡ ከርሷም ብሉ፡፡ ችግረኛ ድሃንም አብሉ፡፡
29
ከዚያም (እንደ ጠጉርና ጥፍር ያሉትን) ትርፍ አካላቸውንና ዕድፋቸውን ያስወግዱ፡፡ ስለቶቻቸውንም ይሙሉ፤ በጥንታዊውም ቤት ይዙሩ፡፡
30
(ነገሩ) ይህ ነው፡፡ የአላህንም ሕግጋት የሚያከብር ሰው እርሱ ጌታው ዘንድ ለእርሱ በጣም የተሻለ ነው፡፡ የቤት እንስሳትም (ግመል ከብት በግና ፍየል) በናንተ ላይ (እርም መሆኑ) ከሚነበብላችሁ በስተቀር ለእናንተ ተፈቅዳላችኋለች፡፡ ከጣዖታትም ርክሰት ተጠንቀቁ፡፡ ሐሰትንም ቃል ራቁ፡፡
Sonraki 30 ayet →