1
ምስጋና ለአላህ ለዚያ መጽሐፉን በውስጡ መጣመምን ያላደረገበት ሲሆን በባሪያው ላይ ላወረደው ይገባው፡፡
2
ቀጥተኛ ሲሆን ከእርሱ ዘንድ የኾነን ብርቱን ቅጣት ሊያስፈራራበት፣ እነዚያንም በጎ ሥራዎችን የሚሠሩትን ምእመናን ለነሱ መልካም ምንዳ ያላቸው መኾኑን ሊያበስርበት፤ (አወረደው)፡፡
3
በእርሱ ውስጥ ዘለዓለም የሚቆዩበት ሲኾኑ (ያላቸው መኾኑን)፡፡
4
እነዚያንም «አላህ ልጅን ይዟል» ያሉትን ሊያስፈራራበት (አወረደው)፡፡
5
ለእነሱም ለአባቶቻቸውም በርሱ ምንም እውቀት የላቸውም፡፡ ከአፎቻቸው የምትወጣውን ቃል ምን አከበዳት! ውሸትን እንጂ አይናገሩም፡፡
6
በዚህም ንግግር (በቁርኣን) ባያምኑ በፈለጎቻቸው ላይ በቁጭት ነፍስህን አጥፊ ልትሆን ይፈራልሃል፡፡
7
እኛ ማንኛቸው ሥራው ያማረ መኾኑን ልንፈትናቸው በምድር ላይ ያለን ሁሉ ለእርሷ ጌጥ አደረግን፤
8
እኛም በእርሷ ላይ ያለውን (በመጨረሻ) በእርግጥ በቃይ የሌለበት ምልጥ ዐፈር አድራጊዎች ነን፡፡
9
የዋሻውና የሰሌዳው ባለቤቶች ከተዓምራቶቻችን ሲሆኑ ግሩም መሆናቸውን አሰብክን
10
ጎበዞቹ ወደ ዋሻው በተጠጉና «ጌታችን ሆይ! ከአንተ ዘንድ እዝነትን ስጠን፤ ለእኛም ከነገራችን ቅንን አዘጋጅልን» ባሉ ጊዜ (አስታውስ)፡፡
11
በዋሻውም ውስጥ የተቆጠሩን ዓመታት በጆሮዎቻቸው ላይ መታንባቸው፡፡
12
ከዚያም ከሁለቱ ክፍሎች ለቆዩት ጊዜ ልክ ያረጋገጠው ማንኛው መሆኑን ልናውቅ አስነሳናቸው፡፡
13
እኛ ወሬያቸውን በአንተ ላይ በእውነት እንተርካለን፡፡ እነሱ በጌታቸው ያመኑ ጎበዞች ናቸው፡፡ መመራትንም ጨመርንላቸው፡፡
14
(በንጉሣቸው ፊት) በቆሙና «ጌታችን የሰማያትና የምድር ጌታ ነው፡፡ ከእርሱ ሌላ አምላክን አንገዛም፡፡ ያን ጊዜ (ሌላን ብናመልክ) ወሰን ያለፈን (ንግግር) በእርግጥ ተናገርን፡፡» ባሉ ጊዜ ልቦቻቸውን አጠነከርን፡፡
15
«እነዚህ ሕዝቦቻችን ከእርሱ ሌላ አማልክትን ያዙ፤ (እውነተኞች ከኾኑ) በእነርሱ ላይ ግልጽ ማስረጃን ለምን አያመጡም በአላህም ላይ ውሸትን ከሚቀጣጥፍ ይበልጥ በዳይ ማነው» (አሉ)፡፡
16
«እነርሱንና ያንን ከአላህ ሌላ የሚግገዙትን በተለያችሁ ጊዜ ወደ ዋሻው ተጠጉ፡፡ ጌታችሁ ለእናንተ ከችሮታው ይዘረጋላችኋልና፤ ከነገራችሁም ለእናንተ መጠቃቀሚያን ያዘጋጅላችኋል» (ተባባሉ)፡፡
17
ፀሐይንም በወጣች ጊዜ ከዋሻቸው ወደ ቀኝ ጎን ስታዘነብል ታያታለህ፡፡ በገባችም ጊዜ እነርሱ ከእርሱ በሰፊው ስፍራ ውስጥ ኾነው ሳሉ ወደ ግራ በኩል ትተዋቸዋለች፡፡ ይህ ከአላህ ተዓምራቶች ነው፡፡ አላህ የሚያቀናው ሰው ቅኑ እርሱ ብቻ ነው፡፡ የሚያጠመውም ሰው ለርሱ አቅኝን ረዳት አታገኝለትም፡፡
18
እነሱም የተኙ ሆነው ሳሉ (ዓይኖቻቸው በመከፈታቸው) ንቁዎች ናቸው ብለህ ታስባቸዋለህ፡፡ ወደ ቀኝ ጎንና ወደ ግራ ጎንም እናገላብጣቸዋለን፡፡ ውሻቸውም ሁለት ክንዶቹን በዋሻው በር ላይ ዘርግቷል፡፡ በእነሱ ላይ ዘልቀህ ብታይ ኖሮ የምትሸሽ ኾነህ በዞርክ ነበር፡፡ ከእነሱም በእርግጥ ፍርሃትን በተመላህ ነበር፡፡
19
እንዲሁም በመካከላቸው እንዲጠያየቁ ቀሰቀስናቸው፡፡ ከእነሱ አንድ ተናጋሪ «ምን ያክል ቆያችሁ» አለ፡፡ «አንድን ቀን ወይም የቀንን ከፊል ቆየን» አሉ፡፡ «ጌታችሁ የቆያችሁትን ጊዜ ልክ ዐዋቂ ነው፡፡ ከዚህችም ብራችሁ ጋር አንዳችሁን ወደ ከተማይቱ ላኩ፡፡ ከምግቦቿ የትኛዋ ንጹሕ መሆኗንም ይመልከት፡፡ ከእርሱም (ከንጹሑ) ምግብን ያምጣላችሁ፡፡ ቀስም ይበል፡፡ በእናንተም አንድንም ሰው አያሳውቅ» አሉ፡፡
20
«እነሱ በእናንተ ላይ ቢዘልቁ ይቀጠቅጧችኋልና፡፡ ወይም ወደ ሃይማኖታቸው ይመልሷችኋል፡፡ ያንጊዜም በፍጹም ፍላጎታችሁን አታገኙም» (ተባባሉ)፡፡
21
እንደዚሁም የአላህ ቀጠሮ እርግጠኛ መሆኑን ሰዓቲቱም በርሷ ጥርጣሬ የሌለ መሆኑን ያውቁ ዘንድ በእነርሱ ላይ (ሰዎችን) አሳወቅን፡፡ (አማኞቹና ከሓዲዎቹ) ነገራቸውን በመካከላቸው ሲከራከሩ (የሆነውን አስታውስ፤ ከሓዲዎቹ)፡- «በእነሱ ላይም ግንብን ገንቡ» አሉ፡፡ ጌታቸው በእነሱ ይበልጥ ዐዋቂ ነው፡፡ እነዚያ በነገራቸው ላይ ያሸነፉት (ምእመናን) «በእነሱ ላይ በእርግጥ መስጊድን እንሠራለን» አሉ፡፡
22
በሩቅ ወርዋሪዎች ሆነው (በጥርጣሬ) «ሦስት ናቸው፤ አራተኛቸው ውሻቸው ነው» ይላሉ፡፡ «አምስት ናቸው፤ ስድስተኛቸው ውሻቸው ነውም» ይላሉ፡፡ «ሰባት ናቸው፤ ስምንተኛቸውም ውሻቸው ነው» ይላሉም፡፡ «ጌታዬ ቁጥራቸውን ዐዋቂ ነው፡፡ ጥቂት (ሰው) እንጂ አያውቃቸውም» በላቸው፡፡ በእነሱም ነገር ግልጽን ክርክር እንጂ (ጠልቀህ) አትከራከር፡፡ በእነሱም ጉዳይ ከነሱ (ከመጽሐፉ ሰዎች) አንድንም አትጠይቅ፡፡
23
ለማንኛውም ነገር «እኔ ይህንን ነገ ሠሪ ነኝም» አትበል፡፡
24
«አላህ የሻ እንደ ሆነ (እሰራዋለሁ)» ብትል እንጂ፡፡ በረሳህም ጊዜ ጌታህን አውሳ፡፡ «ጌታዬም ከዚህ ይበልጥ ለቀጥታ የቀረበን ሊመራኝ ይከጀላል» በላቸው፡፡
25
በዋሻቸውም ውስጥ ሶስት መቶ ዓመታትን ቆዩ፡፡ ዘጠኝንም ጨመሩ፡፡
26
«አላህ የቆዩትን ልክ ዐዋቂ ነው» በላቸው፡፡ የሰማያትና የምድር ምስጢር የእሱ ብቻ ነው፡፡ እርሱ ምን ያይ! ምን ይሰማም! ለእነርሱ ከእርሱ በቀር ምንም ረዳት የላቸውም፡፡ በፍርዱም አንድንም አያጋራም፡፡
27
ከጌታህም መጽሐፍ ወደ አንተ የተወረደውን አንብብ፡፡ ለቃላቶቹ ለዋጭ የላቸውም፡፡ ከእርሱም በቀር መጠጊያን በፍጹም አታገኝም፡፡
28
ነፍስህንም፤ ከእነዚያ ጌታቸውን ፊቱን (ውዴታውን) የሚሹ ኾነው በጧትና በማታ ከሚግገዙት ጋር አስታግስ፡፡ የቅርቢቱንም ሕይወት ሽልማት የምትሻ ሆነህ ዓይኖችህ ከእነሱ (ወደ ሌላ) አይለፉ፡፡ ልቡንም እኛን ከማስታወስ ያዘነጋነውን ፍላጎቱንም የተከተለውን ነገሩም ሁሉ ወሰን ማለፍ የሆነውን ሰው አትታዘዝ፡፡
29
«እውነቱም ከጌታችሁ ነው፡፡ የሻም ሰው ይመን፤ የሻም ሰው ይካድ» በላቸው፡፡ እኛ ለበደለኞች አጥሯ በእነሱ የከበበ የኾነችውን እሳት አዘጋጅተናል፡፡ (ከጥም) እርዳታንም ቢፈልጉ እንደ ዘይት ዝቃጭ ባለ ፊቶችን በሚጠብስ ውሃ ይረዳሉ፡፡ መጠጡ ከፋ! መደገፊያይቱም ምንኛ አስከፋች!
30
እነዚያ ያመኑና መልካም ሥራዎችንም የሠሩ እኛ ሥራን ያሳመረን ሰው ምንዳ አናጠፋም፡፡
Sonraki 30 ayet →