1
አ.ለ.ረ (አሊፍ ላም ራ) ይህቺ (ሱራ) ጥበብ ከተመላው መጽሐፍ (ከቁርኣን) አንቀጾች ናት፡፡
2
«ሰዎችን አስፈራራ፡፡ እነዚያንም ያመኑትን ለእነሱ ከጌታቸው ዘንድ መልካም ምንዳ ያላቸው መኾኑን አብስር» በማለት ከነርሱው ወደ ኾነ አንድ ሰው ራእይን ማውረዳችን ለሰዎች ድንቅ ኾነባቸውን ከሓዲዎቹ፡- «ይህ በእርግጥ ግልጽ ድግምተኛ ነው» አሉ፡፡
3
ጌታችሁ ያ ሰማያትንና ምድርን በስድስት ቀኖች ውስጥ የፈጠረ አላህ ነው፡፡ ከዚያም ነገሩን ሁሉ የሚያስተናብር ሲኾን በዐርሹ ላይ (ስልጣኑ) ተደላደለ፡፡ ከእርሱ ፈቃድ በኋላ ቢኾን እንጂ አንድም አማላጅ የለም፡፡ እነሆ! አላህ ጌታችሁ ነውና ተገዙት፤ አትገሰጹምን
4
ሁላችሁም ኾናችሁ መመለሻችሁ ወደ እርሱ ነው፡፡ (ይህም) የተረጋገጠ የአላህ ቃል ኪዳን ነው፤ እርሱ መፍጠርን ይጀምራል፡፡ ከዚያም እነዚያን ያመኑትንና መልካም የሠሩትን በትክክል ይመነዳ ዘንድ ይመልሰዋል፡፡ እነዚያ የካዱትም ይክዱት በነበሩት ነገር ለነርሱ ከፈላ ውሃ የኾነ መጠጥና አሳማሚ ቅጣት አላቸው፡፡
5
እርሱ ያ ፀሐይን አንጻባራቂ ጨረቃንም አብሪ ያደረገ ነው፡፡ የዓመታትን ቁጥርና ሒሳብን ታውቁ ዘንድም ለእርሱ መስፈሪያዎችን የለካ ነው፡፡ አላህ ይህንን በእውነት እንጂ (በከንቱ) አልፈጠረውም፡፡ ለሚያውቁ ሕዝቦች አንቀጾችን ያብራራል፡፡
6
ሌሊትና ቀን በመተካካታቸው አላህም በሰማያትና በምድር ውስጥ በፈጠረው ሁሉ ለሚጠነቀቁ ሕዝቦች ምልክቶች አሉ፡፡
7
እነዚያ መገናኘታችንን የማይፈሩ ቅርቢቱንም ሕይወት የወደዱ በእሷም የረኩ እነዚያም እነሱ ከአንቀጾቻችን ዘንጊዎች የኾኑ፡፡
8
እነዚያ ይሠሩት በነበሩት ምክንያት መኖሪያቸው በእሳት ውስጥ ነው፡፡
9
እነዚያ ያመኑና መልካም ሥራዎችን የሠሩ ጌታቸው በእምነታቸው ምክንያት (የገነትን መንገድ) ይመራቸዋል፡፡ ከሥራቸው ወንዞች ይፈስሳሉ፡፡ በመጠቀሚያ ገነቶች ውስጥ ይኖራሉ፡፡
10
በእርሷም ውስጥ ጸሎታቸው ጌታችን ሆይ! ጥራት ይገባህ (ማለት) ነው፡፡ በእርሷ ውስጥ መከባበሪያቸውም ሰላም መባባል ነው፤ የመጨረሻ ጸሎታቸውም ምስጋና ለዓለማት ጌታ ይሁን (ማለት) ነው፡፡
11
አላህ ለሰዎች ደግን ነገር ለማግኘት እንደ መቻኮላቸው (አጥፋን ሲሉት) ክፉን ነገር ቢያስቸኩል ኖሮ ጊዜያቸው ወደነሱ በተፈጸመ ነበር፡፡ እነዚያንም መገናኘታችንን የማይፈሩትን በጥመታቸው ውስጥ የሚዋልሉ ሲኾኑ እንተዋቸዋለን፡፡
12
ሰውንም ጉዳት ባገኘው ጊዜ በጎኑ ላይ ተጋድሞ ወይም ተቀምጦ ወይም ቆሞ ይለምነናል፡፡ ጉዳቱንም ከእሱ ላይ በገለጥንለት ጊዜ ወደ አገኘው ጉዳት እንዳልጠራን ሆኖ ያልፋል፡፡ እንደዚሁ ለድንበር አላፊዎች ይሠሩት የነበሩት ሥራ ተሸለመላቸው፡፡
13
ከእናንተ በፊት የነበሩትንም የክፍለ ዘመናት ሰዎች መልክተኞቻቸው በማስረጃዎች የመጧቸው ሲኾኑ በበደሉና የማያምኑም በኾኑ ጊዜ በእርግጥ አጠፋናቸው፡፡ እንደዚሁ ተንኮለኞችን ሕዝቦች እንቀጣለን፡፡
14
ከዚያም እንዴት እንደምትሠሩ ልንመለከት ከእነሱ በኋላ በምድር ላይ ምትኮች አደረግናችሁ፡፡
15
አንቀጾቻችንም ግልጽ ኾነው በእነርሱ ላይ በተነበቡላቸው ጊዜ እነዚያ መገናኘታችንን የማይፈሩት ከዚህ ሌላ የሆነን ቁርኣን አምጣልን ወይም ለውጠው ይላሉ፡፡ እኔ ከራሴ በኩል ልለውጠው አይገባኝም፡፡ ወደእኔ የሚወርደውን እንጂ አልከተልም፡፡ እኔ ከጌታዬ ባምጽ የታላቁን ቀን ቅጣት እፈራለሁ በላቸው፡፡
16
አላህ በሻ ኖሮ በእናንተ ላይ ባለነበብኩትም (አላህ) እርሱን ባላሳወቃችሁም ነበር፡፡ በእናንተም ውስጥ ከእርሱ በፊት (ምንም ሳልል) ብዙን ዕድሜ በእርግጥ ኖሬአለሁ፤ አታውቁምን
17
በአላህም ላይ እብለትን ከቀጣጠፈ ወይም በአንቀጾቹ ከአስተባበለ ይበልጥ በዳይ ማን ነው እነሆ አመጸኞች አይድኑም፡፡
18
ከአላህም ሌላ የማይጎዳቸውን የማይጠቅማቸውንም ይግገዛሉ፡፡ «እነዚህም አላህ ዘንድ አማላጆቻችን ናቸው» ይላሉ፡፡ «አላህን በሰማያትና በምድር ውስጥ የማያውቀው ነገር ኖሮ ትነግሩታላችሁን» በላቸው፡፡ ከሚያጋሩት ሁሉ ጠራ፤ ላቀም፡፡
19
ሰዎችም አንድ ሕዝብ እንጂ ሌላ አልነበሩም፡፡ ተለያዩም፡፡ ከጌታህ ያለፈች ቃልም ባልነበረች ኖሮ በእርሱ በሚለያዩበት ነገር በመካከላቸው በእርግጥ (በቶሎ) በተፈረደ ነበር፡፡
20
በእርሱ ላይም ከጌታው የሆነች ተዓምር ለምን አትወረድለትም ይላሉ፡፡ «ሩቅ ነገርም ሁሉ የአላህ ብቻ ነው፡፡ ተጠባበቁም፤ እኔ ከናንተ ጋር ከሚጠባበቁት ነኝና» በላቸው፡፡
21
ሰዎችንም ካገኛቸው ጉዳት በኋላ እዝነትን (ዝናብና ምቾትን) ባቀመስናቸው ጊዜ ወዲያውኑ ለእነሱ በተዓምራቶቻችን (በማላገጥ) ተንኮል ይኖራቸዋል፡፡ አላህ ቅጣተ ፈጣን ነው፡፡ «መልክተኞቻችን የምትመክሩትን ነገር በእርግጥ ይጽፋሉ» በላቸው፡፡
22
እርሱ (አላህ) ያ በየብስና በባሕር የሚያስኬዳችሁ ነው፡፡ በመርከቦችም ውስጥ በሆናችሁና በእነርሱም በመልካም ነፋስ በርሷ የተደሰቱ ኾነው (መርከቦቹ) በተንሻለሉ ጊዜ ኀይለኛ ነፋስ ትመጣባታለች፡፡ ከየስፍራውም ማዕበል ይመጣባቸዋል፡፡ እነሱም (ለጥፋት) የተከበቡ መሆናቸውን ያረጋግጣሉ፡፡ (ያን ጊዜ) አላህን ከዚህች (ጭንቀት) ብታድነን በእርግጥ ከአመስጋኞቹ እንሆናለን ሲሉ ሃይማኖትን ለርሱ ብቻ ያጠሩ ሆነው ይለምኑታል፡፡
23
በአዳናቸውም ጊዜ እነሱ ወዲያውኑ ያለ አግባብ በምድር ላይ ወሰን ያልፋሉ፡፡ እናንተ ሰዎች ሆይ! ወሰን ማለፋችሁ (ጥፋቱ) በነፍሶቻችሁ ላይ ብቻ ነው፡፡ (እርሱም) የቅርቢቱ ሕይወት መጠቀሚያ ነው፡፡ ከዚያም መመለሻችሁ ወደኛ ነው፡፡ ትሠሩት የነበራችሁትንም ሁሉ እንነግራችኋለን፡፡
24
የቅርቢቱ ሕይወት ምሳሌ ከሰማይ እንዳወረድነው ውሃ፣ በእርሱም ሰውና እንስሳዎች ከሚበሉት የምድር በቃይ ተቀላቅሎበት (እንደ ፋፋ) ምድርም ውበትዋን በያዘችና ባጌጠች ጊዜ ባለቤቶችዋም በርሷ ላይ እነርሱ ቻዮች መኾናቸውን ባሰቡ ጊዜ ትእዛዛችን ሌሊት ወይም ቀን መጥቶባት ትላንት እንዳልነበረች የታጨደች እንዳደረግናት ብጤ ነው፡፡ እንደዚሁም ለሚያስተነትኑ ሕዝቦች አንቀጾችን እናብራራለን፡፡
25
አላህም ወደ ሰላም አገር ይጠራል፡፡ የሚሻውንም ሰው ወደ ቀጥተኛው መንገድ ይመራል፡፡
26
ለእነዚያ መልካም ለሠሩት መልካም ነገርና ጭማሪም አላቸው፡፡ ፊቶቻቸውንም ጥቁረትና ውርደት አይሸፍናቸውም፡፡ እነዚያ የገነት ሰዎች ናቸው፡፡ እነርሱ በውስጧ ዘውታሪዎች ናቸው፡፡
27
ለእነዚያም ኃጢአቶችን ለሠሩት የኃጢኣቲቱ ቅጣት በብጤዋ አለቻቸው፡፡ ውርደትም ትሸፍናቸዋለች፡፡ ለእነሱ ከአላህ (ቅጣት) ጠባቂ የላቸውም፡፡ ፊቶቻቸው ከጨለመ ሌሊት ቁራጮች እንደ ተሸፈኑ ይኾናሉ፡፡ እነዚያ የእሳት ሰዎች ናቸው፡፡ እነርሱ በውስጧ ዘለዓለም ነዋሪዎች ናቸው፡፡
28
ሁሉንም የምንሰበስባቸውን ከዚያም ለእነዚያ ለአጋሩት እናንተም ተጋሪዎችሁም ስፍራችሁን ያዙ የምንልበትን ተጋሪዎቻቸውም እኛን ትገዙ አልነበራችሁም የሚሉዋቸው ሲኾኑ በመካከላቸው የምንለይበትን ቀን (አስታውስ)፡፡
29
«(ጣዖታቶቹ ለእኛ) ከመገዛታችሁ በእርግጥ ዘንጊዎች ለመኾናችንም በእኛና በእናንተ መካከል የአላህ መስካሪነት በቃ» (ይሏቸዋል)፡፡
30
በዚያ ቀን ነፍስ ሁሉ ያሳለፈችውን ሥራ ታውቃለች፡፡ (አጋሪዎች) ወደ አላህም እውነተኛ ወደ ሆነው ጌታቸው ይመለሳሉ፡፡ ከእነሱም ይቀጣጥፉት የነበሩት ነገር ይጠፋቸዋል፡፡
Sonraki 30 ayet →